The Book is Available to Order Online Now!
የደራሲው ማስታወሻ
የአንድ እናት ልጆች፣
በአስተሳሰብ ተጣልተው፣
በአመለካከት ተለያይተው፣
የሚያስታርቅ ጠፍቶ፣
የእብድ ገላጋይ በዝቶ፣
“የደራሲው ማስታወሻ” የተባለው የተስፋዬ ገብረአብ መፅሃፍ ከላይ በሰፈሩት የበአሉ ግርማ ስንኞች ትረካውን ይጀምራል። ከዚያ በሁዋላ መንደርደር እንጂ ማቆም አይቻልም።
በርግጥም የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ትርምስ የመፅሃፉ ማእከላዊ ነጥብ ይመስላል። የአንድ እናት ልጆች በአመለካከት ተለያይተናል። የእብድ ገላጋይ መብዛቱም እውነት ነው። እናም “የደራሲው ማስታወሻን” የሚያነብ ሰው “የት ነው ያለነው?” ብሎ ራሱን መጠየቁ አይቀርም። ሃገሪቱን የሚመሩትን ሰዎች በፍፁም እንደማናውቃቸውም መገንዘብ ይቻላል።
ደራሲው በመግቢያው እንዲህ ይለናል፣
“እኛ የዚህ ዘመን ሃበሾች እንዴት እየኖርን፣ እንዴት እናስብ እንደነበር ለመጪው ትውልድ ልናቆይለት ይገባል። ይህችን ጣጣዋ ያላለቀ ሃገር የሚረከባት አዲሱ ትውልድ፣ ከኛ የፖለቲካ ድንቁርና ተምሮ የተሻለ ስርአትና ዘመን ይቀይስ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”
የደራሲው ማስታወሻ ላይ በርካታ ሰዎች ተዳስሰዋል።
መለስ ዜናዊ እና ስዬ አብርሃን ጠጋ ብለን እናያቸዋለን። ስብሃት ነጋ በጨረፍታ ይዳሰሳል። የጄኔራል ሳሞራ የኑስ ሰብእና አስገራሚ ነው። የስዩም መስፍን የጋብቻዎች ታሪክ “ወይ ጉድ” ያሰኛል። ገብሩ አስራት ያስደምማል። ባጫ ደበሌ “ደስተኛው ጄኔራል” በሚል ርእስ ተወዳጅ ሆኖ ቀርቦአል። ዳዊት ዮሃንስ በሚያስቅ መንገድ ተገልፆአል። የአባዱላ ገመዳ ጄኔራል ጀቤ እና ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ የውስጥ ገበና ከምንጊዜውም በላይ ፍርጥርጥ ብሎ ለፀሃይ ተጋልጦአል። የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትና ምርጫ 97ም በተለየ አቅጣጫ መረጃ ቀርቦባቸዋል።
“የደራሲው ማስታወሻ” በጨረፍታም ቢሆን በርካታ ስሞችን ያነሳል።
ዋለልኝ መኮንንና ማርታ አሟሟታቸው ብቻ ሳይሆን ማን ተኩሶ እንደገደላቸው ጭምር ተጠቁሞአል። አስመሮም ለገሰና የገዳ ስርአት ድንቅ ታሪክ ነው። የሙሉጌታ አለምሰገድና የሲአይኤ ግንኙነት ያመራምራል። አንዳርጋቸው ፅጌና በረከት ስምኦን (በስብሰባ ላይ)፣ ተፈራ ዋልዋና ብርሃኑ ነጋ፣ ታምራት ላይኔ በጭፈራ ዘመን፣ የክንፈ ገብረመድህን የመጠጥ ቤት ድብድብ፣ አክሊሉ ሃብተወልድና ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ አህመድ ግራኝና በረከት ስምኦን፣ አለማየሁ እሸቴና ንዋይ ደበበ... እያለ ይቀጥላል...
የቁንድዶ ፈረሶች ትዝ ይሏችሁዋል? አሁን ደግሞ የቀዌሳ ታሪክ። ደራሲው ሙሉጌታ ሉሌን እዚህም በተለየ ሁኔታ ያነሳዋል። በአሉ ግርማ፣ ሃዲስ አለማየሁና ብርሃኑ ዘርይሁንም አሉ። “ዘርና ዘርማንዘር” በሚል ርእስ ደራሲው የአፍሪቃን ቀንድ ጎሳና ዘር በሚያዝናና መልክ ቀልዶበታል። ”የደራሲው ማስታወሻ” ባህር ነው። በአፃፃፍ ጥበብ፣ በመረጃና በተነባቢነቱ ከቀዳሚው ይበልጥ እንደሁ እንጂ አይንስም።
የደራሲው ማስታወሻ እንደ ቀዳሚው መፅሃፍ በስነግጥም የተዋበ ነው። ደበበ ሰይፉ፣ ዮሃንስ አድማሱና ፑሽኪን የአንበሳ ድርሻ ይወስዳሉ። ማሞ ውድነህ የተረጎሟት ድንቅ ግጥም ለምርጫ 97 ማስዋቢያ ሆናለች። ስብሃት ገብረእግዚአብሄር፣ አበራ ለማ እና ታገል ሰይፉ አሁንም የማር ጠብታቸውን ያቃምሱናል። ገብረክርስቶስ ደስታ፣ መንግስቱ ለማ፣ ዮፍታሄ ንጉሴ፣ ከበደ ሚካኤል እና ሌሎችም....
ደራሲው እንደተለመደው ከደብረዘይት ይነሳና ደቡብ አፍሪቃና ዱባይን ከውስጥ ገልጦ ያሳየናል። ደብረዘይትን ምድረ ገነት አድርጎ አቅርቦአታል። ዛሬ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉት ብርሃኑ ነጋ እና ግርማ ብሩ ሁለቱም ደብረዘይት ላይ ከነጫጭ ርግቦች ጋር እየተጫወቱ ማደጋቸውን ያነሳል። ከእርግቦች ጋር ተጫውተን አድገንበታል የሚለውን ሃይቅ በስእላዊ ቃላት አቅርቦታል - ምስሉ በአይናችን እስኪታይ ድረስ። “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” ላይ የኬንያዎቹ ዱባለና ወርቁ የማይረሱ የሳቅ ተዋናዮች ነበሩ። እዚህ ደግሞ ፈቃዱ በረዳ እና ደምሴ ፖለቲከኛው የፕሪቶሪያ ዋና ኮሜዲያን ሆነው ብቅ ይላሉ። ደረጄና ሃብቴ ለህዝብ ያላቀረቧቸው የፖለቲካ ቀልዶችም ተካተዋል። ተክሉ ተክላይ አንድ ቦታ ብቻ ብቅ ይላል።
“የደራሲው ማስታወሻ” የፖለቲካ መፅሃፍ ብቻ ሊባል አይችልም። ልክ እንደ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” እዚህም ከጥቂት በላይ የስደትና የፍቅር ታሪኮች አሉ። እየሳቅን እናዝናለን። እያዘንን እንስቃለን።
ደራሲው በመግቢያው እንዲህ ይለናል፣
“...በኔ በኩል የጋዜጠኛነት ግዴታዬን እየተወጣሁ ነው። የአይን ምስክሮች የገለፁልኝን ለመጪው ትውልድ የማስረከብ ሃላፊነት አለብኝ ብዬ አምናለሁ። ወደፊትም የሙያው ስነምግባር በሚፈቅድልኝ ደረጃ እገፋበታለሁ። ጓደኞቼ ሆይ! ገና ብዙ እፅፋለሁ!! “ምናገባኝ” ወይም “ጎመን በጤና” ብዬ የምተወው ጉዳይ የለም። የሃገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል። ‘ጎመን በጤና’ የሚለው ዘፈንም የማደንዘዣ መርፌ ነው። እኛ ከክብርና ከኩራታችን ጋር የተፈጠርን ሙሉ ሰዎች ነን። በመሆኑም እንደ ሃበሻ ውሻ ሳይሆን እንደ ሃበሻ ሰው ለመኖርና ለመሞት እንመጥናለን።”
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በመቅድሙ መፅሃፉን እንዲህ ሲል ጥሩ ገልፆታል፣
“....የደራሲው “ማስታወሻዎች” ልብ ወለድ አይደሉም፡፡ እውነተኛ ታሪኮች ናቸው። አብዛኞቹ ገፀባህርያት በህይወት ያሉ ናቸው። መፅሃፉን ማንበብ ስንጀምር ግን እንደማንኛውም ቀልብ የሚሰርቅ የልቦለድ ድርሰት ትረካው ይዞን ይነጉዳል፡፡ ከመፅሃፉ አንድ ምእራፍ የጀመረ ሰው ሳይጨርሰው ለማስቀመጥ በጣም ይቸገራል፡፡ ጠዋት ስራ መግባት ያለበት ሰው ማታ መፅሃፉን እንዲጀምረው አልመክረውም...”